የባህረሐሳብ ቀመር
ባህረሐሳብ ከ 2 የግእዝ ቃላት የተገኘ ሲሆን ባህር ማለት ዘመን ሲሆን ሐሳብ ማለት ደግሞ ቁጥር ማለት ነው በዚህም ምክኒያት ባህረሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው።
ባህረሐሳብን የቀመረው የእስክንድሪያ ሊቀ ጻጻስ የነበረው ቅዱስ ዲሜጥሮስ ነው።
ባህረሐሳብ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የዘመን መቁጠሪያ ቀመር ሲሆን ባህረሐሳብን በመጠቀም የ አመቱ(ለምሳሌ 2016ዓ.ም) በአላት ምን ቀን እንደሚውሉ, አጽዋማት በምን ቀን እንደሚገቡ ለማስላት ይጠቅማል።
ይህንንም በቀላሉ ለማወቅ በ BIBEL Apps የቀረበውን ባህረሐሳብ መተግበሪያን መጠቀም ይችላሉ በመተግበሪያው በመጠቀም ከላይ የተጠቀሱትን ስሌቶች በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ።
በዚህ ጽሁፍ በባህረሐሳብ ተጠቅመን የ 2016ዓ.ም በአላት ምን ቀን እንደሚውሉ, አጽዋማት በምን ቀን እንደሚገቡ ማወቅ እንደምንችል እንማራለን።
የ 2016ዓ.ም አመተ አለም
አመተ አለም ማለት ክርስቶስ ከ ቅድስት ድንግል ማርያም ተውልዶ አለምን ከማዳኑ በፊት የነበረውን 5500 ዘመን (አመት ፍዳ, አመተ ኩነኔ, ወይም ዘመነ ብሉይ) እና የምንፈልገውን አመተምህረት በመደመር ማወቅ እንችላለን።
አመተአለም = 5500 + አመተምህረት(2016ዓ.ም)
አመተአለም = 5500 + 2016
አመተአለም = 7516
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም አመተአለም 7516 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም መጠነራብዒት
መጠነራብዒት አመተአለምን(7516) ለ 4 በማካፈል ማወቅ እንችላለን።
መጠነራብዒት = አመተአለም(7516) / 4
መጠነራብዒት = 7516 / 4
መጠነራብዒት = 1879
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም መጠነራብዒት 1879 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም ወንጌላዊ
የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እያንዳንዱን አዲስ አመት ወንጌልን በጻፉ እራት ወንጌላውያን ትሰይማለች።
የአመቱን ወንጌላዊ ለማወቅ አመተአለምን ለ 4 በማካፈል ቀሪው 1 ከሆነ ማቴዎስ, 2 ከሆነ ማርቆስ, 3 ከሆነ ሉቃስ, 0 ወይም ቀሪ ከሌለው ዮሐንስ ይሆናል።
ወንጌላዊ = አመተአለም(7516) / 4
ወንጌላዊ = 7516 / 4
ወንጌላዊ = 1879 ደርሶ 0 ይቀራል።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም ወንጌላዊ ዮሐንስ ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም አዲስ አመት
አዲስ አመት የሚውልበትን ቀን ለማወቅ አመተ አለምን እና መጠነራብዒት ደምረን ለ 7 በማካፈል ቀሪው 0 ከሆነ ሰኞ, 1 ከሆነ ማክሰኞ, 2 ከሆነ ረቡዕ, 3 ከሆነ ሃሙስ, 4 ከሆነ አርብ, 5 ከሆነ ቅዳሜ, 6 ከሆነ እሁድ ይሆናል።
አዲስ አመት = (አመተአለም + መጠነራብዒት) / 7
አዲስ አመት = (7516 + 1879) / 7
አዲስ አመት = 1342 ደርሶ 1 ይቀራል።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም አዲስ አመት ማክሰኞ ይውላል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም መደብ
አመተአለምን ለ 19 ስናካፍል ቀሪው መደብ ይባላል።
መደብ = አመተአለም(7516) / 19
መደብ = 7516 / 19
መደብ = 395 ደርሶ 11 ይቀራል።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም መደብ 11 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም ወንበር
ከ መደብ ላይ አንድን ስንቀንስ የምናገኘው ወንበር ይባላል።
መደብ 0 ከሆነ ወንበር 18 ይሆናል።
ወንበር = መደብ - 1
ወንበር = 11 - 1
ወንበር = 10
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም ወንበር 10 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም አበቅቴ
ወንበርን በ 11 አባዝተን ለ 30 ስናካፍል የምናገኘው አበቅቴ ይባላል።
አበቅቴ = (ወንበር * 11) / 30
አበቅቴ = (10 * 11) / 30
አበቅቴ = 110 / 30
አበቅቴ = 3 ደርሶ 20 ይቀራል።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም አበቅቴ 20 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም መጥቅዕ
ወንበርን በ 19 አባዝተን ለ 30 ስናካፍል የምናገኘው መጥቅዕ ይባላል።
መጥቅዕ = (ወንበር * 19) / 30
መጥቅዕ = (10 * 19) / 30
መጥቅዕ = 190 / 30
መጥቅዕ = 6 ደርሶ 10 ይቀራል።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም መጥቅዕ 10 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም ጥንተዖን
አመተአለም እና መጠነራብዒትን ደምረን ለ 7 አካፍለን ከቀሪው ላይ አንድ ስንቀንስ የምናገኘው ጥንተዖን ይባላል።
ጥንተዖን = ((አመተአለም + መጠነራብዒት) / 7) - 1)
ጥንተዖን = ((7516 + 1879) / 7) - 1)
ጥንተዖን = (9395 / 7) - 1)
ጥንተዖን = 1 - 1
ጥንተዖን = 0 ይሆናል።
ጥንተዖን 0 ከሆነ 7 እናደርገዋለን።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም ጥንተዖን 7 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም በአለመጥቅዕ
መጥቅዕ ከ 14 በላይ ከሆነ በ መስከረም ከ 14 በታች ከሆነ በጥቅምት ይሆናል።
የ 2016ዓ.ም መጥቅዕ 10 ነው 10 ከ 14 በታች ስለሆነ በአለመጥቅዕ በጥቅምት ይሆናል።
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም በአለመጥቅዕ በጥቅምት ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም መባጃሃመር
መጥቅዕ እና መጥቅዕ የዋለበትን እለት ተውሳክ ስንደምር የምናገኘው መባጃሃመር ይባላል።
የእለታት ተውሳክ
ሰኞ ------------------ 6
ማክሰኞ ------------------ 5
ረቡዕ ------------------ 4
ሃሙስ ------------------ 3
አርብ ------------------ 2
ቅዳሜ ------------------ 8
እሁድ ------------------ 7
መባጃሃመር = መጥቅዕ + መጥቅዕ የዋለበት እለት ተውሳክ
መባጃሃመር = 10 + ቅዳሜ(8)
መባጃሃመር = 18
ስለዚህ የ 2016ዓ.ም መባጃሃመር 18 ይሆናል ማለት ነው።
የ 2016ዓ.ም ዓጸፈወርህ
የምንፈልገውን ወር በ 2 አባዝተን የምናገኘው ዓጸፈወርህ ይባላል።
ለምሳሌ 23/5/2016 ዓ.ም
ወር ጥር(5ኛው ወር)
ዓጸፈወርህ = ወር * 2
ዓጸፈወርህ = 5 * 2
ዓጸፈወርህ = 10
ስለዚህ የ ጥር ወር ዓጸፈወርህ 10 ይሆናል ማለት ነው።
አጽዋማት የሚገቡበትን እና በአላት የሚውሉበትን እለት ለማወቅ ተውሳኩን ከመባጃሃመር ጋር ደምረን ከ 30 ከበለጠ ለ 30 እያካፈልን እናገኛለን።
የበአላት እና አጽዋማት ተውሳክ
ስቅለት ------------------ 7
አብይ ጾም ------------------ 14
ደብረዘይት ------------------ 11
ሆሳዕና ------------------ 2
ትንሳኤ ------------------ 9
ርክበካህናት ------------------ 3
እርገት ------------------ 18
ጸራቅሊጦስ ------------------28
ጾመ ሃዋርያት ------------------ 29
ጾመ ድህነት ------------------ 1
የ 2016 አመተምህረት አብይ ጾም መች እንደሚገባ እንመልከት።
የ 2016ዓ.ም መባጃሃመር 18 ነው
የአብይ ጾም ተውሳክ 14 ነው።
አብይ ጾም = (ተውሳክ + መባጃሃመር) / 30
አብይ ጾም = (14 + 18) / 30
አብይ ጾም = 32/30
አብይ ጾም = 1 ደርሶ 2 ይቀራል።
ስለዚህ በ 2016ዓ.ም አብይ ጾም መጋቢት 2 ሰኞ ይገባል።
የ 2016 አመተምህረት ነነዌ ጾም መች እንደሚገባ እንመልከት።
የ 2016ዓ.ም መባጃሃመር 18 ነው
ነነዌ ተውሳክ የለውም(መባጃሃመር) ነው። ስለዚህ በ 2016ዓ.ም የነነዌ ጾም የካቲት 18 ሰኞ ይገባል።
የ 2016 አመተምህረት ትንሳኤ መች እንደሚውል እንመልከት።
የ 2016ዓ.ም መባጃሃመር 18 ነው
የትንሳኤ ተውሳክ 9 ነው።
ትንሳኤ = ተውሳክ + መባጃሃመር
ትንሳኤ = 9 + 18
ትንሳኤ = 27
ስለዚህ በ 2016ዓ.ም ትንሳኤ ሚያዚያ 27 እሁድ ይውላል።
የ 2016 አመተምህረት ሆሳዕና መች እንደሚውል እንመልከት።
የ 2016ዓ.ም መባጃሃመር 18 ነው
የሆሳዕና ተውሳክ 2 ነው።
ሆሳዕና = ተውሳክ + መባጃሃመር
ሆሳዕና = 2 + 18
ሆሳዕና = 20
ስለዚህ በ 2016ዓ.ም ሆሳዕና ሚያዚያ 20 እሁድ ይውላል።
መልካም ዘመን ያድርግልን
Comments
Post a Comment